በአንደኛው ደስታ በሌላኛው ጥርጣሬ ?

በአንደኛው ደስታ በሌላኛው ጥርጣሬ ?

ኦቦ ለማ የሚናገሩትን ቃል ልብ ይበሉ፡፡ ልብን የሚነካ ንግግርዎት አፈር ደሚ እንዳይግጥ ከፈለጉ በተግባር ይታጀብልን፡፡ይህ የሚናገሩለት ህዝብ ” የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ብሎ ከልጁ በላይ ለቃሉ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡

                                                                          by; ግርማው አሸብር

የዛሬ ምልከታና የግል አመለካከቴን ለማካፈል ሳስብ በጥያቄ ምልክት ጀመርሁት፡፡ ምክንያቱም ሰሞንኛው የኦሮማራ ነገር ሁለት ፊት አድርጎናል፡፡ በአንደኛው ደስታ በሌላኛው ጥርጣሬ፡፡ የምን ጥርጣሬ

images (1)

ካላችሁ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” ነውና ተረቱ በኀላ ሳንጠረጥር አምነን ፣ የተሰገጸጠንን ሁሉ ሳናኝክ ከዋጥነው መረታትና የሆድ ቁርጠቱም ከባድ ነው፡፡

#ኦቦለማ የሚናገሩትን ቃል ልብ ይበሉ፡፡ ልብን የሚነካ ንግግርዎት አፈር ደሚ እንዳይግጥ ከፈለጉ በተግባር ይታጀብልን፡፡ ይህ የሚናገሩለት ህዝብ ” የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ብሎ ከልጁ በላይ ለቃሉ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡

የአገሪቱን ፖለቲካ ለምንም አላማ ይሁን ለምን በኪስዎ ይዘው እንደፈለገዎ እያሾሩት ነው፡፡ እርስዎ ባህር ዳር ከተማ የአማራ ህዝብን በአዳራሽ ሰብስበው ስለኢትዮጵያ ” ለቀባሪ ማርዳት” እንዲሉ ሰብከው አስጨብጭበዋል፡፡ ህዝቡ የሚያጨበጭብልዎት የውስጥ ምኞቱን ፣ የአንጀት ርሃቡን ከእርስዎ አንደበት መስማቱ እንጅ ቅኔው ብርቁ ሆኖ አይደለም፡፡ ብርቅ የሆነበት የሞተለትን የአንድነት ቃል ይዘው ከአንድነት አፍራሹ ስርዓት በመፈጠርዎ እየተደናገረውም እየገረመውም ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሱስ የምትሆነው ባህል እና ማህበራዊ እሴቷ ሲጠበቅላት ፣ የዜግነት ክብር ብለን የምንዘምረው የህዝቡ መዝሙር እውነት በተግባር ሲሆን ነው፡፡ ካለበለዚያ ኢትዮጵያ ዋናው (ኦሮጅናሉ)ቅኔ ከመወድስ እስከ ጉባኤ ቃና ሲዘረፍላት ኖራለች፡፡ ግን አቆርቋዥ ባለበት አገርን ቅኔ ብቻውን ለሃገር ፍቅር በቂ አይደለም፡፡ ቅኔ ብቻውን ሲሆን ከፍቅርም አልፎ ሱስ ፣ ከሱስነት ተርፎ ወፈፍ የሚያደርገው የርሃብ ላይ ስካር ነው የሚመስለው፡፡

በባዶ ሆዳችን ፖለቲካ ሆያ ሆየ ብንጫወት በርሃቡ ላይ አረቂ እንደጠጣ ጀብራሬ ንግግራችን ሁሉ የጎዳና ላይ እብድ ንግግር ነው የሚሆነው፡፡ አገራችን የዕውነት መነሳትና የእውነት የቃል ኪዳን ንግግር ትሻለች፡፡ በአንድነት የዘላለማችን ጠኔ ለመውጣት የሚያስችል ፖሊሲ እና የህዝብ ንቃተ ህሌና ከሚፈጥረው መጠነ ሰፊ ፍላጎት ጋር የሚያራምድ የህዝብ አስተዳደር ምስረታ እንሻለን፡፡ በየትኛውም ጥፋት ውስጥ የቆየ አጥፊ ሁሉ የአገሪቱን የወደፊት እጣፋንታ ህዝብ እንዲወስን እድሉን መስጠት አለበት፡፡ ያ ሲሆን የነበረው ሃጥያት በዚህ አድራጎት ይሻራል፡፡ አብረን በይቅርታ እንቀጥላለን፡፡

ካልሆነ ግን እንደለመደብን ሟችና ገዳይ ተሰዳጅና አሳዳጅ ሆነን በቀርፋፋው ታሪካችን ማዝገማችን ግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡ የሰብዓዊ መብትና ለህዝብ ጥቅም ድምፃቸውን የሚያሰሙ የአገር ልጆችን የሚያበረታታ እንጅ ድምፃቸው እንዲጠፋ የሚያሳድድ አምባገነን አስተዳደር መጨረሻው በስልጣን ላይ ሆኖ ማንጎለጀት እንጅ ያተረፈው ጥቅም እንደሌለ እያየን ነው፡፡

አቶ ለማ መገርሳ ህዝብ የራበውንና የተጠማውን ኢትዮጵያዊነት ድምፅ ይዘው ተነስተው በየመድረኩ አማርኛ እስከሚጨንቀው በኢትዮጵያዊነት ቃላት እየተቀኙ ነው፡፡ ሸጋ ነው ግን ወያኔ አፈር ልሳ በአቶ ለማ በኩል የእባብ ሸንኮፏን አራግፋ ለመነሳት የምታደርገው ጥረት ነው የሚሉ ተንታኞችም አሉ፡፡ ይህንን እንዴት ውሸት ነው እንበል!?

ሁለት ባንዴራና የድንበር ወሰን ፣ የህዝብ መዝሙር እና ህገመንግስት እንዲኖረራቸው ያደረጋችኀቸውን ህዝቦች እንዴት አንድነት ለማጠናከር እየሰራን ነው ትሉናላችሁ!?

ሁለቱ ህዝቦች ሁለት ሰንደቅ አላማ እየያውለበለቡ ፡ ልጆቻቸው በየትምህርት ቤቱ የተለያዩ መዝሙሮችን እየዘመሩ እንዴት ለአንድነት እየሸራን ነው ትሉናላችሁ? ወደ ባህርዳር ስተትሄዱ በሶስት ባንዴራ ያሸበረቀ ባነር በማንገብ እንዴት አንድ ነን ማለቱ ቀላል ሆነ? ከወሬና ምርጥ ቃላትን ዋጋ ከማሳጣት በፊት ሁለቱ ህዝቦች የልዩነት ክልላዊ ሰንደቁን ጥለው የአገሪቱን ሰንደቅ እያውለበለቡ ስለአንድነት ማስዘመር ምኑ ላይ ከባድ ነበር?

እንደ መጀመሪያው ገፅ የመጀመሪያዋ አንቀፅ (Paragraph) የተሄደው ሁለሉ ሸጋ ነው፡፡ ግን እያየን ያለነው የአቶ ገዱም ይሁን የአቶ ለማ ንግግር ውበት ብቻ ነው፡፡ ሸሞንሟና ንግግር ስሜትን ገዢ ነው፡፡ “ለወሬ የለውም ፍሬ” ነውና ነገሩ አንዲት የተግባር እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ አንድ መዝሙርና አንድ ሰንደቅ አላማ የነበረውን ህዝብ የከፋፈላችሁት እናንተ ናችሁ እና ወደነበርንበት የተዋበ አንድነት መልሱን፡፡ ህዝቡ በተለይ የተጠቀማችሁት የአዛውነንቶች ስበብስብ አገሪቱ ምን እንደነበረችና እንዴት እንዳደረጋችኀት ያውቃል፡፡ መስሚያውን ይስጣችሁ፡፡

አሁን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ከተፈለገ አንድ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያ ሰማይ መውለበለብ አለበት፡፡ አንድ ህገመንግስት መርቀቅ አለበት፡፡ አንድ መዝሙር መዘመር አለብን፡፡

Comments