አማርኛ ቋንቋና ኢትዮጵያ

 

አማርኛ ቋንቋና ኢትዮጵያ


በየትኛውም ቋንቋ የትኛውንም የግል ሃሳብና አመለካከት ማንፀባረቅ ፤ ለምንም አላማ መጠቀም መቻል የአማርኛ ቋንቋ ባህሪ ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ተፈጥሮ ነው፡፡images (3)

ከአራት አመታት በፊት ደቡብ ክልል አማርኛ እንደሁለተኛ ቋንቋ ሳስተምር ቋንቋውን መናገርና መግባባት የሚችሉት ተማሪዎች ያላቸው በራስ የመተማመን ስሜትና ደስታ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ባደረግሁት የዳሰሳ ጥናትም ምክንያቱ የአገሪቱን የስልጣኔ ቋንቋ መናገር በመቻላቸው እና ከከተማ የመጣ ሰው ጋር መግባባት በመቻላቸው እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፡፡ ያው እንግሊዘኛ የሚፈጥረው አይነት ስሜት፡፡

ነገር ግን ከወደ ትልልቅና በእድሜ ከፍ ያሉ በተለይም ከወረዳ አመራርና ምናምን ጀምሮ ፣ አንዳንድ አካባቢም ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ቋንቋውን የማጥላላት ነገር አለ፡፡ ይሔ በጥቅሉ የተሳሳተ ግንዛቤና የወቅቱ የሽቀላ ፖለቲካ የሰራው መርዝ ነው፡፡ በዚህ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ጥናት ባይደረግም የነፍጠኛ ቋንቋ እየተባለ በደፈናው ጭፍን ጥላቻ ተነዝቶበታል፡፡

ህፃናት በአፍ መፍቻቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲማሩ የካናዳ ፣ አሜሪካ ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎቹም አገራት በ1960ዎቹ አካባቢዎችና ቀደም ብሎም ጀምረው ለጊዜው መንገራገጮች ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በምርምሮችና ማስታረቂያ ፖሊሲዎች በመቅረጽ ስኬታማ መሆናቸውን የቋንቋና ማህበረሰብ ተመራማሪዎች (sociolingust) የጥናት ውጤት ያሳያል፡፡
እንደኛ አገር ህፃናትን በአፍ መፍቻቸው አካባቢያቸውን እንዲያውቁ/ጠንካራ ግንዛቤ እንደኖራቸው በሚል ጠቃሚ መሰረት የተጀመረው የትምህርት ፖሊሲ አተገባበሩ ዘረኝነትን መሰረት አድርጎ በህጻናት አእምሮ እንዲሰርጽ የሚያደርግ ነው፡፡

ለዚህም ማሳያው ነፍጠኛንና እና ተግባሩ መኮነን ሌላ ወያኔ ወለድ ተላላፊ በሽታ ቢሆንም በዚህ ፖሊሲ ውስጥ ፣ በአስተዳደራዊ መዋቅርና ድንብርትና በመከፋፈየነት ቋንቋና ዘር መኖሩ ትልቅ የአገር በካይ ቫይረስ ሆኗል፡፡

ቋንቋ በአፈጣጠሩ እንጅ በአገልግሎቱ ሰዋዊ እንጅ ጎሳዊ አገልግሎት ላይ የተወሰነ አይደለም፡፡ ማንም ሰው የሆነ ሁሉ በፍላጎቱ የሚለምደው /የሚማረው/ከቤተሰቦቹ ወይም ከማህበረሰቡ የሚወርሰው ነው፡፡

የኮንሶኛ ቋንቋ ልክ እንደ ኦሮምኛ ቋንቋ በአማርኛ ፊደላት መፃፍ ጀምረው ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኀላ የአገረኛውን አማርኛ ፊደል ጥለው በእንግሊዝኛ ቀይረውታል(ለዚህም ትልቁን የተሳሳተ ድርሻ የወሰደው ከኮንሶ የተወለደ የዲላ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የስነልሳን አስተማሪ የብሔረሰቡ ምሁራችን ያሉት አንድ ሰው እና ወያኔ አመጣሽ ካድሬዎች ናቸው፡፡ ) ይህን የብሄረሰብ አቋም የወሰዱትና የተገበሩት የብሔር አስተዳደር ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ያደረጉት ነው፡፡ ለጊዜው ምክንያት የተደረገው የኩሽ ቋንቋዎች አንዳንድ ድምፆች ወካይ ፊደል ስለሌላቸው ነው የሚል ስነልሳናዊ ምክንያትን አስቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን በትግርኛ ፣ በጉራግኛ ፣ በአገውኛ(የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ ነው)  እንደምናየው ተኪ ድምፆችን መቅረፅ ፣ ማዳቀል ፣መፍጠርና አገልግሎት ላይ ማስገባት አማርኛ ፊደላትን (የሳባ ፊደላትን) ለፅሁፍ አገልግሎት መጠቀም ተችሏል፡፡
ለምሳሌ እንደ(|ቐ|ቑ|ቓ|ቔ|ቕ|ቖ|ቛ| ፣ |ሇ| ፣ |ኇ|ኈ|ኊ|ኋ|ኌ|ኍ| ፣ |ኧ| ፣|ዏ|፣ |ዯ|ፇ )

የአገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንግሊዘኛ ከሚያስተምረኝ የአገር ውስጥ ቋንቋን አገውኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ ትግሬኛ ከብዙዎች ውስጥ አንዱን ብማር ኖሮ ለኔም ለአገሪቱም በጠቀመኝ ነበር፡፡ ሌሎች አገሮችም እንግሊዘኛን የሚፈልግ በግል ጥረቱ ወይም በግል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሰልጠኛ እንዲያዳብሩ ነው የሚመክሩት፡፡ ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ማንነታቸውም ይሰጣሉ፡፡ ለዲፕሎማሲ ግንኙነት በማደግ ላይ ያሉ እንደ ቻይና ፣ ህንድ ፣ ኢንዶኔዥያ ያሉ አገራትም ቋንቋና ባህላቸውን የአገራቸውን ነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለመሆን ለሄደ ሁሉ ያስተምራሉ፡፡ በየአለማቱ ባሉ ኤንባሲዎቻቸውም ውስጥ የቋንቋ ባህልና ቱሪዝም ዲፕሎማሲ ዘርፍ በነፃ ያስተምራሉ፡፡ ይሄ በትልቁ ቁና ራሳቸውን ሰፍረው ለሌላው ማቅናት(ማካፈል)ሲችሉ ነው፡፡ እንደኛ የአንድ ጎሠ ቀየ መራመድ በማይችል የቋንቋና ባህል አስተሳሰብ ይህንን ለማድረግ ለጊዜው ከባድ ይመስላል፡፡ መጀመሪያ ከጎሳ ዳፍንታችን አይናችንን መግለጥ አለብን፡፡

ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከአማርኛ አለፍ ሲል ገጠር ለባለአገሩ ለባለአገሩ ወገናችን መንግስት ከውጭ የሚያስገባቸውና ለህክምና የሚቀርቡ መድሃኒቶች የአጠቃቀም መምሪያ በእግሊዘኛ ወይም የተሰሩበት/በመጡበት አገር ቋንቋ ነው፡፡ አብዛኛዎቹን የአገር ውስጥ ተመራች መድሃኒቶችን ይጨምራል፡፡ የአገራችን ሃኪሞችም መድሃኒት ማዘዣ ወረቀት ለታካሚው ሲሰጡ በእንግሊዝኛ ያም እንዳይነበብ ውንግርግር (የዶክተር ፅሁፍ የሚባለው) አድርገው ነው፡፡ ይህ ማለት የቋንቋን አገልግሎት አለመረዳትና አገሪቱም ስለቋንቋ ወጥ የሆነ አገራዊ (harmonized policy) ባለመኖሩ ነው፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎች Elic (English language improvement center ) የሚባሉ ቤተሙከራ ሁሉ ያላቸው ተሿሚ ሃላፊ ያላቸው ጽ/ቤቶች አሉ፡፡ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ግን(ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ሳይጨምር) ማንም ትኩረት ሰጥቶ ከማዳበር ይልቅ ለማጥፋት መሯሯጥ ላይ ነው ዘመቻው፡፡

ይህ ከላይ እንዳልሁት የችግሩ መነሻ ያልተጠና ቋንቋንና ጎሳን መሰረት ያደረገው ፖለቲካችን ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ ሊዳብር የሚችለውም ሆነ ሊከስም የሚችለው በህዝቦች ፍላጎትና ጥላቻ አይደለም፡፡ አገር ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች አለም አቀፋዊ ሆኖ የስልጣኔውን አለምም ተላምዶ በጎግል ላይ የሚገኝ ካለምንም ድጋፍ አድራጊ ተቋም የገነነ ቋንቋ ፣ በርካታ ታሪካዊ ድርሳናትና ታሪኮችን የሰነደ መክተቢያ ነው፡፡

ቋንቋ ማሰቢያም ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ለትምህርት በምኖርበት አገር ቋንቋቸውን በፍላጎቴ ተምሬ እየተግባባሁት/እየተገለገልሁበት ያለ መሳሪያየ አድርጌዋለሁ፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ ግን ከአፍ መፍቻየ ቋንቋ በተጨማሪ ሁለት የውጭ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆኔ እና በአገሬ ውስጥ ከተፈጠሩና ከሚነገሩ በመቶ ከሚቆጠሩ ቋንቋዎች አንዱንም ባለማወቄ ለራሴ ሃፍረት ይሰማኛል፡፡

ይህ ስሜት ያደረብኝ በራሴ ሳንባ መተንፈስ ስጀምር ነው፡፡ ማህበረሰቡም ይሁን የአገሪቱ መንግስት ይህንን መተንፈስም ሆነ የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን እድሉን አልፈጠረልኝም፡፡ ነገር ግን ተወልጄ ካደግሁበት ገጠር እዚያ ጫካ ውስጥ በሰባት አመቴ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ላከልኝ፡፡ እዛው ዝንጀሮ ጠባቂ (ሰብልን ከዝንጀሮ መከላከል) እየለሁ ጀምሮ እንግሊዘኛን ብቻየን ተማርሁት፡፡ በቃ ይሄው ነው የኛው ነገር፡፡
የአካባቢየ የቄስ ተማሪዎች በግዕዝ ቋንቋ ፣ እኔ በእንግሊዘኛ(ለጉራ የሚሆን ብቻ አላጣም ነበር) ለቁራሽ ልመና ሲመጡ እንጋጠም ነበር፡፡ እኔ ግዕዙን ትርጉሙን ባላውቀውም አነበው ነበር ግን ድምጸት ፣ ተነሽ ወዳቂውን ስለማላውቀው ሰድበውኝ/ተሳልቀውብኝ ይሄዳሉ፡፡ ምክንያቱም እንድማር የተፈረደብኝ ማንንም እዚያ አካባቢ በማላናግርበት ቋንቋ እንጂ እነዚየሠን አመስጣሪ ተቀኝዎች ጋር እንድግባባ የሚጋብዝ እድል አልነበረኝም፡፡

ወደቀደመ ነገሬ ስመለስ በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ ስለኪነ-ጥበብና ስለቋንቋ መስሚያዋ እንግሊዘኛ ላይ ብቻ ሆኗል፡፡ ከዚህ ክብ ጓዳ ወጣ ብለን ስናስብ ግን የአገር ባህል መበከል መተላለፊያ ባክቴሪያው መጤ ቋንቋ ነው፡፡ ለዚህ መጤ ነገር ደግሞ መዳኛ ሊበጅለት ይገባዋል፡፡ መጤም የሚመጣው በዕጭ ንግድና ግንኙነት የተነሳ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው የበርካታ ጎሳና ቋንቋ ባለፀጋ ብትሆንም የአገር ውስጥ ዜጎችን አንድ አድርጎ ማስተሳሰር የሚችል ቋንቋ (ካለው ታሪካዊ እድልም) የተሻለ መፍጠን የቻለው እና ብቸኛው ሆኖ የቀጠለው አማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ ይህንንም ከቋንቋ ባህሪ አንፃር ብቻ በመተንተን የዚህን ቋንቋ ልምድና ርዕዮት ፤ ያለፈባቸውን ዘመናት በመዳሰስ ሌሎቹ ቋንቋዎቻችን እንዳይጠፉና እንደአቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ወሳኝ ምሁራዊ እርምጃ ነው የሚል ሃሳብ ማስተጋባት እፈልጋለሁ፡፡
ስለዚህ እንደአንድ አገራዊ ዝምድና መተሳሰሪያ ሰንሰለት ከአፍሪካ ብቸኛ ባለፊደሉን ቋንቋ ማሳደግና ከዚህ ቋንቋ የእድገት መነሻ አንፃርም ሌሎች ቋንቋዎችን በማጥናት መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡

የኦሮምኛ ቋንቋ ሰፊ ተናጋሪ ይኑረው አንጅ የአገሪቱን አድማስ የመሸፈን ውስንነቱ ይታወቃል፡፡ በሁሉም የኦሮሞ ህዝቦች አካባቢ አማርኛ ይነገራል፡፡ ወይም በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞችና አቅራቢያ ቦታወች አማርኛ ዘር ሳይለይ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ከሆነ ምዕተ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኦሮምኛም ሆነ ሌሎች ቋንቋዎች ልክ እንደ ሲዳምኛ እና ሶማሊኛ ሰፊ ተናጋሪ ህዝብ የያላቸው ቋንቋዎችን መሳደግ በተጨማሪ ስርዓተ ትምህርት (Extra-curricular)ውስጥ አካቶ ማስተማር እና ማበልጸግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ቋንቋዎች ለማሳደግ በቋንቋው እድገት ላይ ተፅዕኖ አድራሽ ናቸው የተባሉ ነገሮች ነፃ ለማድረግ በጥናትና በምርምር ተቋማት የተረጋገጡ መፍትሄዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ነገር ግን በኦሮምያ አንዳንድ አካባቢዎች እንደምናየው ቀይ ቀለም ይዞ የአገር ውስጥ ቋንቋ ላይ ቀይ ሽብር ማካሄድ በህዝብ ለህዝብ ትስስርም ይሁን በአገር ላይ ትልቅ ጠንቅ ይፈጥራል፡፡ ይህ ተግባር ለምንም ይሁን ለምን አተገባበሩ ግን ደመነፍሳዊ አይነትና ለሌላ ተጓዳኝ አንድምታ የሚጋብዝ በመሆኑ የተፈለገውን ተግባር ለመፈጸም አድማዊ እርምጃ ሳይሆን ምሁራዊ አስተሳሰብ ተጨምርበት ቢከናወን በአብሮ መኖር ላይ ሊያሳድረው የሚችለውን እኩይ ስሜት መቀነስ ይችላል፡፡ የሚመለከተው አካል በተለይ በኦሮሞና የአማራ ብሎም የኦሮሞና የአንድነቱ ፖለቲካ አቀንቃኙ ሃይል ጉዳዩን ሰከን አድርጎ መዳኘት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ማንኛውም ቋንቋ በተፈጥሮው መነሻው ቡድን ነው፡፡ እያደገ ሲሄድ የጎሳ፤ ሰፋ ሲልም ማህበረራዊ ሽፋን እያገኘ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የኔ ነው የሚለው የማህበረሰብ አካል ይኖዋል ማለት ነው፡፡ ባህሉንና እሴቱን ይቀርፅበታል፡፡ በዚህ ውስጥ በጉርብትና ተፅዕኖ ፣ በስደት ፣ በወረራ ፣ በጦርነት ፣ በዘመናዊ ቅኝግዛት(እንግሊዘኛ) ሊዳከም ፣ ሊከሳ ሲበረታበትና አለንልህ የሚለው ተናጋሪ ካለገኘም እንደ ጋፋትኛ ሊሞት ይችላል፡፡

Amharic is a Semitic language spoken in Ethiopia. It is the second-most spoken Semitic language in the world, after Arabic, and the official working language of Ethiopia. Amharic is also the official or working language of several of the states within the federal system and in USA.

በመጨረሻም ከታች ያያያዝሁት ምስል በሙሉ በጎግል ፕሌይ ላይ የምናገኛቸው በሺህ የሚቆጠሩ የአማርኛ መማሪያ ስልቶች ሲሆኑ በዘመናዊ የአንድሮይድ ስልኮች የተሰሩ ናቸው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ተራማጅና ማንመም የማያስቆመው የአፍሪካ ምሉዕ ቋንቋ ብቸኛው ኢተትዮጵያዊ መሆኑ ነው፡፡

የኪነጥበብና ቋንቋ የተጠና ትልቅ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ሃገርን አንድ አድርጎ የሚማግር የቋንቋ ባህልና ኪነ-ጥበብ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ 

ልብ ይስጠን!!!

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ13ኛው እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአማርኛ ቋንቋ ቀደምት ዘመናት መካከል የተሻሉ መረጃዎች የተገኙበት ዘመን ነው፡፡ በአንድ በኩል አማርኛ በዛጔዬና እንደገና በመጣው ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥታት› ውስጥ ልሳነ መንግሥት ሆኖ የወጣበት መሆኑን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም አሠራርን በተመለከተ ለተዘጋጀው ጉባኤ የቀረበ ጽሑፍ ያሳያል፡፡
 
 
የአማርኛ ቋንቋ በሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ዳግም ምሥረታ ወቅት ‹ልሳነ መንግሥት› ይሁን እንጅ ‹ልሳነ ጽሑፍ› የሆነው በእነዓፄ ይስሐቅ እና ዓፄ ዓምደጽዮን ዘመነ ንግሥና እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የቋንቋውን አነሳስ ከዘመነ ንግሥና አስተሳስሮ ማየት አማርኛ በአገልግሎት ጅማሮውም የቤተ መንግሥት ቋንቋ ሆኖ ነበር ማለት አይደለም፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ግዕዝን ተክቶ የቤተ መንግሥት ቋንቋ ከመሆኑ በፊት የሠራዊት እና የሕዝብ መግባቢያ ቋንቋ ስለነበር የቋንቋው መሠረት ሕዝብና ሠራዊት እንጂ ቤተ መንግሥት አልነበረም፡፡ በሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ላለው ስርጭቱ የሕዝብ እና የሠራዊት ቋንቋ መሆኑ ሳይጠቅመው እንዳልቀረም የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ፡፡
 
አማርኛ መላው ኢትዮጵያን በስፋት ሲያገለግል የቆየና እያገለገለ ያለ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ቅርፁ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ሰዋዊ ባሕርይ የሚያሳይ መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይም በቅርብ ዓመታት ለቋንቋው የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ሀገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ላይ የአደጋ ስጋት ፈጥሯል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህም በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ማጠቃለያ ፈተና አለመካተቱንና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ትኩረት አለማግኘቱን እንደማሳያነት ይቀርባሉ፡፡
 
ባለፉት ዓመታት በፌዴራል ሥርዓቱ ክልሎች የእኔ ለሚሉት ቋንቋ ትኩረት ሰጥተው ቋንቋዎቻቸውን ለማበልጸግ ጥረት አድርገዋል፡፡ “ነገር ግን …” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን መምህርና ተመራማሪው ባየ ይማም (ፕሮፌሰር) ስለቋንቋው ትኩረት ማጣት ሲናገሩ፤ “ነገር ግን አማርኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ በመሆኑ የተለየና የእኔ ብሎ ተቋም እና አቋም ይዞ የሚያበለጽገው ወገን አልነበረውም፡፡”
 
“የሀገሪቱ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ በየትኛውም ቋንቋ ትምህርት እና ፈተና እንዳይሰጥ አይከለክልም” ያሉት ፕሮፌሰር ባየ ለአንድ ቋንቋ የተለየ የአካባቢ ‘ታርጋ’ መስጠት በአፈፃፀም ላይ ግድፈት እንዲፈጠር ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
 
እንደፕሮፌሰር ባየ ገለፃ አሁን አማርኛ የተለየ የትንሳኤ ዘመን አለው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በርካታ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ሕዝቡ ለቋንቋ ያለው አመለካከት በጎ እና ልጆቻቸውም አማርኛን እንዲማሩ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ‘እንደሀገር አንድ መግባቢያ ቋንቋ አስፈላጊ መሆኑን ሕዝቡ ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጽሑፍ እና በተደራሽነት የዳበረ አቅም ያለው ቋንቋ መሆኑ አግዞታል’’ ብለዋል ምሁሩ፡፡
 
ኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ ኖሯት እንደማያውቅ ፕሮፌሰር ባየ ተናግረዋል፡፡ ፖሊሲ መኖሩ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ቋንቋዎች የሚያድጉበትንና የሚጠበቁበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ የከተሜነት፣ ትምህርት፣ ኢንዱስትሪ፣ ብዙኃን መገናኛ፣ ብሔራዊነትና ሌሎችንም ለውጦች ተጠቅሞ ከዚህ የደረሰው አማርኛ በሂደት ሀገሪቱ ለሚያስፈልጓት ሀገራዊ መግባቢያ ቋንቋነት ከፖሊሲው ብዙ ተስፋን ይጠብቃል፡፡
 
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Comments