ከአንጀት ከሆነ እንባ አይገድም

 EDIT

ነጻ ሃገር ነኝ በላቸው፡፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ፊደልና ጀግና ህዝብ አለኝ በላቸው፡፡ ያለ ጅሃድ ጦርነት እስልምናን ተቀብላ ባህልና ወጓ ያደረገች የቀደምት የክርስትና ምድር ናት ሃገሬ ስትላቸው ማንነትህ ይገባቸዋል፡፡ ስለ ቡናህና የሰው ልጅ መገኛነቷ ስትነግራቸው፣ ስለታላቁ የአፍሪካ አባት ግርማዊ ራስ ተፈሪ ስትነግራቸው ያኔ አንተ ትገለጥላቸዋለህ፡፡

IMG_3692+

በግርማው አሸብር

ኢትዮጵያዊነት ሸጋ ነው ፡፡  ያኮራል፤ ከሰው በላይ ነው ልዕልናው፡፡  በዚሁ ሩቅ ምስራቅ ኢንዶኔዝያ ሃገር በተዘጋጀ  ግሎባል የባህል ፉስቲቫል ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ተገኝቻለሁ፡፡ ሊኖሩ የሚችሉትን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅሜ ኢትዮጵያን ስወክል ትልቅ ማንነት ተስተጋብቶብኛል ፤ እናንተም ብትሆኑ ኢትዮጵያዊነት ይዋረሳችኋል፡፡

ያው የውርስ ሃገር አይደል ያለን፡፡ ከእነዚያ ታላላቆች የወረስናት፡፡ ከቀማኛዎች እጅ ሳትገባ ህይወት ከፍለው ያወረሱን፡፡ Ethiopia defeated the Italian colonial army in the battle of Adwa. የሚል ጽሁፍ ሳነብ ኢትዮጵያ ቀኝ ሊገዟት የመጡትን ጣሊያኖች ደፍታ መለሠቻቸው ብየ ነው ምረዳው፡፡/ defeated = ደፏቸው ሃሃሃ…

በዝግጅቱ ላይ ከ30 በላይ የዓለም አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ተሳትፈዋል፡፡ ኢንዶኔዥያ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ፓኪስታን ፣ አሜሪካ ፣  ጀርመን፣ ቻይና፣ ባንድላዲሽ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ካምቦጅያ፣ ታይላንድ፣ ቱርኪሚኒስታን ፣ ማሊ፣ ታንዛኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ማዳጋስካር፣ ሆላንድ፣ግብጽ፣ሱዳን፣ፖላንድ፣ አውስትራሊያ፣ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ፣ ራሺያ፣ ቱርኪሚኒስታን እና ለቴሎችም አለኝ ያሉትን መገለጫዎቻቸውን ይዘው ቀረቡ ተሳትፈዋል፡፡

የምግብና አልባሳት፣ የኪነ-ጥበባዊ ስራዎችና ታሪክ በዋናነት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡  በበዓሉ ላይ እኔ በመሀኜቴ ብጫ የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከሌሎች ተሳታፊ ሃገሮች እኩል ሲውለበለብ ማየት መኖሬን እንድወደው እና ትርጉም ያለኝ ሰው መሆኔ በደንብ ይሰርጸኛል፡፡  አንድ ሰው ብቻ ስለተሳተፈ  ኢትዮጵያን በትልቅ የፌስቲቫል መድረክ ላይ ስሟ ሲጠራ ሃገሬን አስጠራሁ የሚል ስሜት ይወራችሁና ኩራት ያጥለቀልቃችኋል፡፡

ኢትዮጵያዊ ስለሆንህ በአቢስንያ ክብር ተጀቡነህ ሲያዩህና ለፎቶ ስትጋበዝ/ስትጠየቅ ደስታ ይፈነቅልሃል፡፡ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት ስትል ስለረሃብና ችግርህ ሚያወሩህ ሰዎች ስለ ማንነትህ ማወቅ ሲጀምሩ ትከበራለህ፡፡ የፓን አፍሪካውን አባት ኔልሰን ማንዴላን ያሰለጠነች ሃገር ናት በላቸው፡፡ ድፍን ጃማይካ ንጉሷን ያመለከላት ሃገር ናት ብለህ እየደጋገመንህ ንገራቸው፡፡ የሬጌው ሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌይ መለኮቱና ልብሱ ያደረጋት አገር እሷ የኔ አገር ናት በላቸው፡፡

 ኢትዮጵያ በክብሯ እንጅ በኢኮኖሚዋ ኑራ ባታውቅም ሃያላን ሃገሮች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ እኛ ደርሰን ካለችበት ልዕልና ካላወረድናት በቀር የልእልናዋን ከፍታ እስካሁን በተዓምር ማንም አልደረሰበትም፡፡

ነጻ ሃገር ነኝ በላቸው፡፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ፊደልና ጀግና ህዝብ አለኝ በላቸው፡፡ ያለ ጅሃድ ጦርነት እስልምናን ተቀብላ ባህልና ወጓ ያደረገች የቀደምት የክርስትና ምድር ናት ሃገሬ ስትላቸው ማንነትህ ይገባቸዋል፡፡ ስለ ቡናህና የሰው ልጅ መገኛነቷ ስትነግራቸው፣ ስለታላቁ የአፍሪካ አባት ግርማዊ ራስ ተፈሪ ስትነግራቸው ያኔ አንተ ትገለጥላቸዋለህ፡፡

የመጣሁት ከረጅሙ ወንዝ መፍለቂያ ምድር ከግዮን ወንዝ ነው በላቸው ይደመሙ፡፡ መለያ ምልክቴ የቃል ኪዳን ማሰሪያው ቀስተ-ዳመና ነው፤ አገሬም ታላቋ አቢሲኒያ ናት፤ የቃል ኪዳን ምድሯ በላቸው፡፡

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡(ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር መዝ67:31) Ethiopia shall soon stretch out her hands unto God.”(Psalms 68:31) የሚለውን ጨምሮ ከ44 በላይ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈችው ሃገሬ ናት ስትላቸው ያኔ ያውቁሃል፡፡ የኢትዮጵያ ስም በታላቁ መጽሃፍ የተከተበው ለኢትዮጵያዊያን ብቻ እንዳልሆነ ይገባቸውና ቀልባቸው ወደ ሚስጥሯ ሃገር ጥልቅና ውስብስብነት ይነጠቃል፡፡ ማናት ኢትዮጵያ ይሉሃል፡፡ እየነገርሃቸው ትርጉሟ ውስብስብ ይሆንባቸዋል፡፡

እያለ……እያለ…….ይቀጥላል፡፡

ሃገረ ኢትዮጵያን በየትኛውም ቦታና ጊዜ እንሰብካለን!!

መድሃኒተ ዓለም ያችን ምድር ይባርክ !!!!

Comments