“ትልቅ ስለነበርን ትልቅ እንሆናለን?”
“ትልቅ ስለነበርን ትልቅ እንሆናለን?”
በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ እና እንዲሁም አንድ ለእናቱ ተብለው የሚታወቁት የ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ አጤ ቴዎድሮስ ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ከዛሬ 199 ዓመት በፊት ተወለዱ።
ከበደ ሚካኤል ጃፓን እንደምን ሰለጠነች በሚለው መጽሃፋቸው ” የዛሬዋ ጃፓን ከዳግማዊ ቴዎድሮሷ ኢትዮጵያ ጋር እኩል በ1855 የኢንዱስተሪውን አቢዮት ተቀላቀሉት፡፡” ሲል ጽፏል፡፡አሁን ጃፓን የሮኬት ማ/ፋሽኖችን እያማረጠች የምዕራቡን አለም በአይኗ ቂጥ የምትመለከት ፣ የአለምን የቴክኖሎጂ ገበያ ቀጥ አድርጋ የተቆጣጠረች ሆናለች፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያም የቴዎድሮስን ራዕይ በእልፍኙ ያሳደገው ዳግማዊ ሚኒልክ ተቀብሎ ሃገሪቱን አዘምኗታል፡፡
፦ የዞረብንን አስማት ባናውቀውም አሁን ከያዘን ቁራኛ ስርዓት ጋር ተዳምሮ “ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን”ን አማረብን ብለን እንዘምራለን፡፡
ሌሎች አገሮች የነበሩበትን ታሪክ አይደለም ዳግም ሊኖሩት ሊያስቡት ትግስት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ኢንዶኔዥያ 350 አመታትን በኔዘርላንድ ቅኝ ግዛት ውስጥ ቆይታለች፡፡ በኀላም ጃፓን አፈር ደሜ አስግጣ ገዝታታለች፡፡ 713 አገር በቀል ቋንቋዎችና በወረራም ይሁን በስልጣኔ ሰበብ ወደአገራቸው የገቡ 6 መጤ ቋንቋዎች አሏት፡፡ ይሁን እንጂ ከነፃነቷ በኀላ ለህዝቦቿ አንድነት ይበጅ ዘንድ የራሷን ብሔራዊ ቋንቋ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች አዳቅላ ፈጥራ በ1945 በማወጅ ከመጀመሪያው ደረጃ ትምህርት አስከ ፍልስፍና ደረጃ ድረስ ታስተምራለች፡፡
ኢትዮጵያ 85 በላይ እውቅና የተሰጣቸው ቋንቋዎች ሲኖሩ ከ120 በላይ አካባቢያዊ ዘየ (ዲያሌክት) ቋንቋዎች ቢኖሯትም ከተቆራኛት ከፋፍለህ እርገጠው ስርዓት የተነሳ ብሄራዊ ቋንቋ የላትም፡፡ በተግባር የብሄራዊነት ተግባሩን ይዞ እያገለገለ ያለው አማርኛ ቢኖርም እስከ ተናጋሪዎቹ እርግጫ የበዛበት ቢሆንም በጎግል ከአለም ታላላቅ ቋንቋዎች እኩል ደረጃ በግፍ በቅቷል፡፡ የስራ ቋንቋ ቢሆንም አደጋ ውስጥ ነው፡፡ በውጭ የትምህርት ፖሊሲና በባዕድ ቋንቋ የትምህርት ስርዓት ተተብትቦ ገና ከጅምሩ የትምህርት ጥራቱ የልጅነት ልምሻ ላይ ነው፡፡
በህዝብ ብዛቷ 260 ሚሊዮን አካባቢ የደረሱ ሲሆን በአለም ደረጃ ደግሞ ቻይና ፣ ህንድና አማሪካን ተከትላ በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በእምነት ደረጃ ከ8 በላይ ሃይማኖቶችን ማለትም እስልምና አገሪቱ የምትታወቅበት ቢሆንም ቡድሂዝም ፣ ሂንዱይዝም ፣ ክርስትና ፣ ኮንፊሽያኒዝም እና ሌሎች በየደሴቶቿ ያሉ ባህላዊ እምነቶችን ጨምሮ ከ300 በላይ ነገዶችን /ብሔረሰቦችን አቻችላና አንድ አድርጋ ይዛ መካከለኛ በሚባል ስልጣኔ ላይ ትኖራለች፡፡
ኢትዮጵያ ክርስተና እና እስልምናን መቶ ሚሊዮን ህዝቦች ያሏት ሲሆን 84 የተለያዩ ነገድ ያላቸው ህዝቦች አቻችላና አንድ አድርጋ ማኖር ተስኗት እርስ በእርስ ማናቆር ፖሊሲን በእስከመገንጠል ህገመንግስት እውቅና ሰጥታ ለየትኛውም መጤም ይሁን ስርዓት አልባ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ግንኙነት የሌላቸው እምነትና ባህል በሯን ክፍት አድርጋ ዝብርቅርቅ ቀለም አልብ የዚህ ወቅቱ ዥንብርብር አገር ሆናለች፡፡
ኢንዶኔዥያ ነፃነቷን ያገኘችው በ1946 ሲሆን በዚያን ጊዜ የባንዱኝ ኮንፈረንስ የሚባለው የኤዥያና አፍሪካ አንድነት ጉባኤ መስራች በመሆን በ1955 ግርማዊነታቸው ቀኅስ አፍሪካን ወክለው በመገኘት “አይዟችሁ በርቱ እኛ የነጻነት ምድር ሰዎች ነን ከጎናችሁ ነን” ብለዋቸው ነበር፡፡ ይሄን ያወቅሁት የዚያን ጊዜ የኢንዶኔዥያዊ ፕሬዝዳንት ሱካርኖ ከቀኀስ ጋር ፎቷቸው በቲሸርት ተሰርቶ የባህልና ታሪካዊ ስጦታ መሸጫ ሱቅ ባገኘሁበት አጋጣሚ ነው፡፡
ስጠይቃቸው ” ኢኒ ኦራንግ ራጃ ኢቱፒያ ዳን ተማን ያንግ ፐርታማ ፕረዝዳንት ኢንዶኔዥያ” ይህ ሰው የኢትዮጵያ ንጉስና የኢንዶኔዥያ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ወዳጅ ነው እንደማለት ነው፡፡ ችግሩ አንዳንዶች ኢትዮጵያን ጃማይካ ውስጥ ያለች አገር ናት አሉኝ ሃሃሃሃ፡፡
ታዲያ የአፍሪካዋን ኢትዮጵያ በጠኔዋ ነው የሚያውቋት፡፡
በነፃነት የኖረች አገር ፣ሊደፍሯት የሞከሩ ወራሪዎቿን አፈር ደሚ ያስጋጠች እና በውርደት አከናንባ የመሰለች ፣ ለሌሎች አገራት ነፃነት ስትለፋ ስትታገል የኖረች አገር ( ማሳያ የኮርያ ዘመቻ) ዛሬ በርዳታ ስንዴና በክርስቶስ ዝናብ ላይ ብቻ ኢኮኖሚዋን ተስፋየ ብላ በመናወዝ ላይ ትኖራለች፡፡
ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!!
ይህ ቃል ውርደታችንን አምነን ከሚመጣው የበለጠ ውርደት በመስጋት ወደነበርንበት የመመለስ አንድምታን/ ስምምነትን የያዘ ነው፡፡
እንዴት?
ትልቅ የነበርነው በአፄዎቹ ዘመን ነው፡፡ ተከብረን ፣ ራሳችንን አስኸብረን ፣ ተፈርተን አስፈርተን ፣ ቱርክ ፣ እንግሊዝ ፣ ሱዳን/ደርቡሽ ፣ ሱልሱላው ጣልያንን አንበርክከን ከዚያም አልፎ የአፍሪካ አገሮችን አንቅተን ቀለማችንን በባንዴራቸው አትመን(ዛሬ የእንግሊዝንና የአሜራካን ባንዴራ ቲሸርትና ጃኬት አድርገው እንደሚለብሱ ራፐር ነኝ ባይ ሸፋፋዎች) ከፍ ብለን ነበር፡፡
ትልቅ ነበርን ? መቼ?
አዎ ነበርን፡፡ በቋራ ፣ በዛጉኤ ፣በአክሱም ፣ በላሊበላ ፣ በፋሲለደስ ፣ በእንጦጦ/አንኮበር ዘመነ መንግስት፡፡
ከዚያስ?
ሰሞኑን አንድ ከማሊ የመጣ ወዳጄ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስተር ስሙ ማነው? አለኝ፡፡ ያው… ነገርሁት፡፡ ሃይለማርያም ደሳለኝ ይባላል አልሁት፡፡ እሱም ሃይለ ስላሴ… ሃይለማርያም … እያለ ሲኩተመተም ከልቤ ሳቅሁ፡፡ ምን እንዳሳቀኝ አልነግራችሁም፡፡ ከዚያ እና አስካሁን ልክ እንደ ብሪታኒያ ” ንግስት ኤልዛቤጥ ” እናንተም ሃይለ የሚል መጠሪያ አላችሁ ማለት ነው? አለኝ፡፡
እኔም ይሄኛው ዝም ብሎ ሃይለማርያም ተብሎ ነው፡፡ እናቱ ያወጣችለት ነው፡፡ ያኛው አንተ የምታውቀው ግን እናቱ ያወጣችለት ተፈሪ መኮንን ሲሆን ሃይለ ስላሴ ስዩመ እግዚአብሄር ወይም በሲመተ-ንግስናው ዕለት በቤተመቅደስ በቃልኪዳን ሹመት ሲቀባ “አገር እና ህዝብንና ፣የህዝቧንም ሃይማኖትና ባህል አስጠብቅለሁ/እጠብቃለሁ” ብሎ የተሰጠው ነው ብዬ ነገርሁት፡፡ የገባው ይመስለኛል፡፡
ቀጠለና የኛ ባንዴራኮ የናንተን ይመስላል አለኝ፡፡ አዎ ልክ ነህ ትልቅ ስለነበርን፡፡ ማሊ ብቻ ሳትሆን እነ ጋና ፣ ሴኔጋል ፣ቤኒን ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ካሜሮን ፣ማዕከላዊ አፍሪካ ፣ ኮንጎ ፣ ሩዋንዳ ፣ ዛየር፣ ቶጎ ፣ ዝምባብዌ… ብዙ አገሮች ቀለማችንን ከቀለማቸው ቀላቆለው ባንዴራቸው አድርገውታል አልሁት፡፡
ትልቅ ስለነበርን ያልከኝ አሁንስ ? አለኝ:: አጣብቂኙ ገርሞኝ እየሳቅሁ አሁንም ነን ኧረ አልሁት፡፡ እኔ ምለው ግን ድንገት የት ናችሁ ስትባሉ የት ነን እያላችሁ ይሆን? ላሊበላ ያን ጊዜ መሰራቱ ሲገርመን አሁንም ታምረኛው የክርስትና አባት ደገሙት፡፡ እና ምን ይሻላል? በየትኛው ዘርፍ ነው የኛ ታላቅነት?
“monolithic rock-cut churches/ሞኖሊቲክ ሮክ-ከት ቸርችስ” እያሉ ፈረንጆች ቃላት እስከሚያጥራቸው የሚፅፉለት ላሊበላ ዛሬም ከተደገመ በሌላው ዘርፍ የጋራ ሃገራዊው ለውጥ ላይ መሻሻል የተሳነን ምን ቢጎለን ነው? ብዙ ጥያቄ አለ እዚህ ጋ!!የላሊበላን ጥበብ አድንቀን ታላቅ ነበርን ካልን ዛሬ ላሊበላ በአንድ መንፈሳዊ አባት ሲገነባ ስላየን ታላቅ ሆነናል ወይም ወደነበርንበት ተመልሰን ይሆን?
ምንድነው የጎደለን ? ምንድነው የምንፈልገውስ?
ከላይ ስለ ኢንዶኔዥያ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ እዚህ አገር ፣ ምግብ ፣ ልብስ ፣ መጠለያ ዜጎች ሃሳባቸው አይደለም፡፡ ትምህርታቸው በአገራቸው ፍልስፍና የተሰላና የተቀመረ ነው፡፡ በዚህ አገር የዶሮ ማምረቻ ተቋማትና የምግብና መጠጥ ማቀነባበርያ ካምፓኒዎች በርካታ ናቸው፡፡ እኛ አገር ዶሮ ጭራ/ፈልሳ አድጋ ነው ለምግብ ያውም አውዳመት ተጠብቆ ጎረቤት ተጠራርቶ ፤ የደስታ ቀን ተመርጦ ነው የምትበላው ፤ እዚህ የሰርክ ምግባቸው ነው/በሌላው አለምም ቢሆን፡፡ ዘወትር ጥዋት በየሬስቶራንቶች ለስላሳ እንደሚከፋፈለው የተበለተ ዶሮ በመኪና አምራች ድርጅቶች ሲያከፋፍሉ ትመለከታላችሁ፡፡
ወዳጆቼ ይሔን ስፅፍ ንፅረቱ ቀላል ሊሆን ይችላል ነገር ግን ወድጄ አይደለም” አንድ ከተፈጠረ የማየት እድል የተነፈገው አይነ ስውር ሰውየ ለሰከንድ ያክል የማየት እድል ይገጥመውና በዚያች ቅፅበት አውራ ዶር ያያል፡፡ ከዚያ ተመልሶ እውር ይሆናል፡፡ ከዚያ በኀላ ሁሉመም ነገር አውራ ዶሮ ይመስለዋል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ዋው እንተና የገዛት መኪና ስታምር ሲሉት ከአውራ ዶር ትበልጣለች ይላል፡፡ የእንተና ፍቅረኛ ቁንጅናዋ እንዴት እንደምተምር ሲነግሩት” ከአውራዶር ታመምራለች ይላል፡፡ ምን ለማለት ነው ኢትዮጵያ ላይ ስንኖር ሁሉም ነገር ገነት ፣ ሁሉም ነገር ሸጋ ፣ እኛ ከአለም አንደኛ የአገር ቁንጮ ብለው እየነገሩን በባዶው ነገር የተጀቦንን ውስጠ ባዶ ደሃዎች ሆነና፡፡
ልጅ ሆኜ ተወልጀ ያደግሁበት ሰፈር በተራራ የተከበበ ረባዳ ቦታ ነው፡፡ ከቆምሁበት 360 ዲግሪ ስሽከረከር የተራራው ዳርቻ ክብ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ትምህርተ ቤት ስገባ መሬት ድንቡልቡል/ክብ ናት ስባል ማረጋገጫየ እሱ ነበር፡፡
አድጌም በአለም ላይ አንደኛው ፓለቲካ ሲባል ኢሃዲግ ፣ ልማት ሲባል ኢሃዲግ ፣ ህገመንግስት ሲባል ኢሃዲግ ፣ ፓርቲ ስባልም ኢሃዲግ ፣ ሸጋ መንግስት ሲባልም ኢሃዲግ ፣ ኢንዱስተሪ ሲባል የሲሚንቶ ፋብሪካ ፣ የጦር ሰራዊት ሲባል መከላከያ ሰራዊት ፣ ምርጥ መሪ ሲባል መለስ ዜናዊ ፣ ስልክ ሲባል Ethio telecom ፣ ቴሌቪዥን ሲባል ኢቲቪ ፣ ጋዜጠኛ ሲባል ተመስገን¡ ፣ ቋንቋ ሲባል እንግሊዘኛ ……እንዲመስለኝ/ን አድርገው ለ27 አመት ያክል ጠፍጥፈውናል፡፡
ትልቅነትን ከተመኘን ወደኀላ መመለስ ወይም ያለፈውን የሚያስመኘን ምን ነክቶን ነው?
……ሊቀጥልም ላይቀጥልም ይችላል::
Comments
Post a Comment