አንድ የአገራችን ምሁር በኦሮምያ እና አማራ ህዝቦች መካከል የነበረውን እና ስላለው የጠበቀ ዝምድና ሲያወራ አያይዞም ስለሚከሰቱ ግጭቶች ተናግሯል፡፡ “በአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል ያለው ከመጋባት ፣ ከማስረግ ፣ አብሮ ሃዘን ደስታን ከመካፈል ውጭ ምንም የልዩነት ታሪክ የለንም፡፡ እንደሚባለው እንኳ አለ ብለን ብናስብ የነበረው ፖለቲካዊ ስርዓት እንጅ ህዝቡን የሚመለከት አይደለም፡፡” ይሄነን ሃሳብ የፅሁፌ መነሻ ያደረግሁት አሁን በየአካባቢው የሚከሰቱ ዘርን ያነጣጠሩ ግድያዎችን …
እያስተዋልን ባለበት ሰዓት መነሻቸው ምንድነው? ገዳይና ተገዳይ ስለምን እንደሚገዳደሉስ ያውቁታል ወይ? ሟች የሚሞትበትን ሰበብ ያውቀዋል ወይ? ገዳይ የሞት ሰይፍ የሚከነዳበትን ምክንያት ያውቀዋል ወይ? ከ1983 በፊትም ሆነ በኀላ የአገራችን ምሁራን በተለይም ስሙን ማስታወስ ያልቻልሁት አንድ ሰው ታሪካዊ ምክሮችን ለሞተው ጠቅላይ ሚኒስተር አካፍለው ነበር፡፡ የምሁሩ ማህበረሰብ የቻለውን ያክል ራሱን በማግለል ፣ በመተቸት ፣ በመቃወም የስርዓቱ አገር አፍራሽነት ተቃውሟል፡፡ መክሯል ዘክሯል፡፡ የዘር ፖለቲካ ዞሮ ዞሮ የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የንጉሱ ስርዓት ጎጃምን ጨፍጭፎ ነበር፡፡ ” ሞጣ ቀራኒዮስ ምነው አይታረስ በሬ ሳላይ መጣሁ ከዚያ እስከዚህ ድረስ ” ተብሎም ተዘምሯል፡፡
ነገር ግን ቂምም ይሁን የተተከለ ቁርሾ ቅሬታ ጎጃም ውስጥ የለም፡፡ ቢኖር እንኳ የአገሪቱን ንጉሳዊ አስተዳደር ማውገዝ እንጅ የሰራዊቱን ዘር ፣ ማንነት ያጥላላ ወይም ለይቶ የተቃወመ አልነበረም፡፡ የሰዓቱን ፖለቲካ በበላይነት የሚጋልብ የበላይ ዘር ስላልነበረ ንጉሱ ተቆጡ ከማለት ውጭ የተለየ ሆኖ ወደ ማህበረሰቡ ጠልቆ ገብቶ መጠፋፊያ አልሆነም ነበር፡፡ ዛሬ አንዱን ሹመኛ ሲያስነጥሰው ዘሩን ቆጥሮ ይማርህ ሲላቸው ሌላኛው በደፋህ የሚልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ መሰረቱ ምንድን ነው? ኢህአዲግ ወይም ገዥው አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባሩ በሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ የተረጋጋ ፖለቲካን መሰረት ማስያዝ ያልቻለው ምን ቢጎለው ነው? ተሃድሶ የሚባለው ቃል ትርጉሙ ሊሸከመው ስላልቻለ ጥልቅ የሚል ተጨምሮበት ህዳሴ አድርገናል ብለው እንኳ እንደገና ወደ ጥልቅ ብጥብጥ አገሪቱ ተጋብዛለች፡፡ ይቺ አገር ከመነጣጠል ሳይሆን ማዕከላዊ አንድነት ከማቋቋም ነው ትርፍ ታገኝ የነበረው፡፡
ታሪካችን ምንን ያሳየን ይሆን? መልካሙን ሰነድ እያቃጠልን ለማጥቆር የምንፈልገውን ዘር እየለየን ፣ የጥላቻ ጆከር እየመዘዝንለት ከርካሹ የፖለቲካ ምድጃ ዳር ተጎልተን ልንሞቅ በማሰብ ፣ በጥል-ቂም በቀል ሃውልት የደገፍነው መከፋፈል(አኖሌ) ፣ ከብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ይልቅ ሁሉም እንደየ ብሔሩ የራሱን ባንዴራ እንዲያውለበልብ ፣ ከአንድነት መዝሙር ይልቅ የራሱን መዝሙር እንዲዘምር ፣ ከአገር ድንበር ይልቅ የክልሎችን ድንበር እንዲያስጨንቀው ወዘተ… ተደርጎ በብዙ የዘረኝነትና ዘመናዊ የመሳፍንትነት ስርዓት ታጅቦ ሊሞቅ የተለኮሰው እሳት ዛሬ ወላፈኑ አላስጠጋ ብሏል፡፡ አጥፍቶ ጠፊ እያደረገ እንደሆነ ከወደነቀምት እየሰማን ነው፡፡
እዚህ ጋ ከወደ ፌስ ቡክ ሰፈር ያገኘኀትን ስንኝ ልጨምርባት፡፡ በይ አንቺም ቅመሺው (ገጣሚው አይታወቅም) ወንድምሽ ሲገደል እንደዚያ የሳቅሽው፣ አጋዚ ደም ሲያፈስ እንዲያ የጨፈርሽው ፣ ከበሮ አነግበሽ እስክስ እስክስት ያልሽው፣ ዛሬ ተራሽ ደርሷል በይ አንቺም ቅመሺው፡፡ መቼም የሰው ቁስል እንደራስ አይሆንም፣ ዛሬ ባንቺ ደርሶ አየሺው ሁሉንም፡፡ እኔ ምልሽ ውዴ ወንድምሽ ሲገደል፣ ህዝብ ሲጨፈጨፍ ሰው ሁሉ ሲበደል፣ ምድር ቃውጢ ሆና ፍትህ ፍትህ ስትል፣ ነግ ለእን ያላልሽው ምን አስበሽ ነበር? በይ አንቺም ቅመሺው ፅጓሽን ተጎንጪ፣ የጠነሰስሽውን የጥላቻ ጥንስስ እየቀዳሽ ጠጪ ግዴለም ተጎንጪ ደርስሽ አትቆጪ ጽጓ አልወድም ብለሽ አትገላፈጪ፡፡ የትግራይ ዝምታ አንድም መስማማት አልያም ለሌሎች ግድ የለሽ መሆን ይመስል ነበር፡፡ የዝምታ ተቃውሞ ስሌለ፡፡ አንዳንድ የደፈሩ ተጋሩዎች አጋዚን የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡
ሞትን በወገን ሞት ላይ የሚያሾፉ ነበሩ፡፡ በህዝብ ፍቅር ላይ የሚያላግጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ዝምታው ጠንካራ ነበር፡፡ እናም በርካታ ወገኖቹን በየቀኑ የሚቀብረው የኦሮሞ እና የአማሪ ህዝብ ወዶ ሳይሆን ቀኑን አክፍተውበት ነው፡፡ መንግስትን ያክል መዋቅር የጥላቻ ማሰልጠኛ ሰነድ አዘጋጅቶ (በተለይ ምንልክ ተኮር) ስልጠና በመስጠት ያጎረመሰው ዘረኝነት እያበላላን በተለይም በአማራ እና በኦሮሞ መካከል ቁርሾው ለአማራው ተወላጅ በግልፅ አላስፈላጊ ዋጋ ሲያስከፍል ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን በተለይም በከፍታ ወይም የክፋት ዘመኑን በጀመርን ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ በቤንሻንጉል ፣በኦሮሞ ፣በሶማሌ ክልሎች በርካታ ወገኖች ሙሉ ዘመናቸውን ከኖሩበት ይዞታቸው ላይ ተገለዋል፡ ተፈናቅለዋል፡፡ ሲነግሩት አይሰሜው ስርዓት ኦሮሞውን በአማራ ላይ ለማዝመት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ሃውልት ቆሞ እንኳ ለዘረኛው ስርዓት ሰለባ ባልሆኑ ተራማጅ ኦሮሞዎች ዘንድ አይወክለንም ብለውታል፡፡ ሃውልቱ ልክ እንደሞተው ጠቅላይ ሚኒስተር መቃብር በፌደራል ፖሊስ እየተጠበቀ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህኛው mission መክሸፍ በኀላ ወደ ሶማሌ ፊቱን በማዞር በኦሮሞ ላይ የግፍ ግፍ ስራ ተሰራ፡፡ ኮርያ እና አሜሪካ ከሚለዋወጡት ዛቻ በላይ በሁለቱ ክልሎች አስተዳደር የቃላት ልውውጡ ያስፈራ ነበር፡፡ ትርፉ ደሀውን ኦሮሞና ሶማሌ አፈናቅሎ የቀን ጎደሎን ከማስቆጠር ያለፈ አይደለም፡፡ ትግራይን ከአማራ አቃቅሮ የበለጠ ለማጋጋል የሽማግሎች እርቅ የሚሉት ጨዋታ በራሱ የረከሰ የቂላቂል ጨዋታው ተጀምሯል፡፡
ስለዚህ ሶማሌው ከኦሮሞው ፣ አማራው ከትግሬውና ከኦሮሞው ፣ ኦሮሞው በዚያ በኩል ከጌዲኦና ሲዳሞው (ጉጅና ጌዲኦ) ተቃቅሮ እየተመለከትን እና ይህንን ከማስታገስ ይልቅ የሚያባብሱ ስውር አጀንዳዎች እያገረሹ መከሰት ጀምረዋል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ አገሪቱ በእውኑ መንግስት ያስፈልጋታል ወይ? “ሊሞቁት የለኮሱት እሳት…” ይሔ ድሮም ይታወቃል፡፡ የአምቦ ወጣቶችን መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ባስጨፈጨፈ ማግስት ከወደ ነቀምት ወለጋ የተሰማው ወሬ አሳዛኝም አሳፋሪም ፣ በባህል እምነታችንም ሆነ በኢትዮጵያችን ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ #መሞትን የሚያወግዝ ፣ አትግደሉን የሚል ነጻነትና ፍትህ የራበው ህዝብ #መግደልን የነፃነት ምርጫ ማድረጉ ያልተሰላ አቢዮት ነው ካልሆነም መሪ አልባ ብጥብጥ ነው፡፡ ልክ እንደበፊቱ ዛሬም ውጉዝ ከመአሪዎስ ብያለሁ፡፡ መንግስት ለምን ገደለ? በመግደል የህዝብ ድምፅ መመለስ አይቻልም፡፡ መኪና አቃጠለ ብሎ ክቡር የሰውን ህይወት በጥይት መቁላት ነውርም አቅመ-ቢስነትም ነው፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ሳይቃጠል በቅጠል የሚለው ላይ ያልተሰራ ስራ የህዝብ አቢዮት ላይ ጥይት መተኮስ እሳት ላይ ቤንዚን ከመጨመር ቢብስ እንጅ አይተናስም እያልሁ እኔም እመክራለሁ፡፡ የአገራችን ጠብ መንጃዎች በሙሉ የአገሩቱ ዳር ድንበርን ለማስከበር የድኝበር አጥር ይሰራባቸው፡፡ መሃል አገር ጠመንጃ ትርጉም አልባ ነው፡፡ መሳሪያ ታጥቆ በወገኑ መሃል የሚኝቀሳቀስ ሰራዊትም በሪሞት ኮንትሮል ከሚያንቀሳቅሱት ግዑዝ ሮቦት የተለየ ስለመሆኑ አጠያያቂ ነው፡፡ በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰውን ሞት ሳወግዝ እንደነበረው ሁሉ የነቀምቱን ኢትዮጵያዊ ወጣት ግድያ አወግዛለሁ፡፡ አሳዛኝም ነው፡፡
ወንድማችን ነፍሱን ይማረው!! ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ትዝብቴ አማራ እየሞተ ስለቴዎድሮስ አድሃኖምና ሮበርት ሙጋቤ ጉዳይ ተንታኝ የነበረና ረፍት ያጣ የትግራይ አንዳንድ ሰዎች ከነቀምቱ አንድ ወጣት ሞት በኅላ ሻማ ልኮሳ ፣ ሞት አውጋዥ ፣ I feel heart break ፣ ዛቻ ድርደራ ምን የወለደው ነው? በህዝቦች አንድነት ላይ ጅብና አህያ እያለ ከመቀሌው የዩኒቨርስቲ አስተማሪ እስከ—- ድረስ ሲሳለቅ የነበረ ዛሬ እነሱ የደገፉት መከፋፈል እንደማንኛውም ወጣት የህዝብ አቢዮት እራት ለሆነ ወጣት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን ፋይዳ አለው? ከአማራው እና ከኦሮሞው ሞት የተለየ ነበር እንዴ የሞተው!? ከሆነ ስንተኛውን ሞት? የሞት ደረጃ አለው? የባህርዳር ወጣት ፣ የአምቦ ፣ የቤንሻንጉል አማራ ፣ የኦሮምያ አማራ ሞት የሰው ልጅ ሞት አልነበረም እንዴ ? ያን ጊዜ ጀምረን ይሔነን መሞት ማውገዝ አልጀመርንም እንዴ እኛ? ያኔ የት ነበራችሁ? ልብ ይስጠን፡፡ ዘሩ ተለይቶ “ና ውጣ አንተ መጤ” ተብሎ ከመገደልና በሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ ቦምብ በባጃጅ ይዞ ሲንቀሳቀስ ተይዞ ከመሞት የትኛው ነው የግፍ ሞት? ከዚህ ልብ ያለው ልብ ይበልና መጻዒው ፍዳ ሳይጠነክር አገሪቱን በብሔራዊ እርቅ አስተካክለን አብረን እንኑርባት ባይ ነኝ፡፡ እንደእኔ ትዝብት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛ ፍትህና ስርዓትን ለመገንባት እስካልተረባረበ ድረስና የጅግና ዘር ፣ የወርቅልጅ ፣ የተጋዳላይ ልጅ እያልን ህዝብ ታግሶት የሩብ ክ/መን እድሜ ለሰጠውና አርጅቶ ሊቆም ምርኩዝ ላጣ ስርዓት የምናደርገው መወለድን መሰረት ያደረገ ውግንና መዘዙ ከሆነው ብሶ ቢቀጥል እንጅ መቆሚያው የት አንደሆነ ለአሁኑ አይታየኝም፡፡ አንዳንዴ ሊሞቁ የለኮሱት ምድጃም ዶግ አመድ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተተከሉ ሃውልቶች ውስጥ አንድም የአንድነትና የፍቅር ሃውልት የለንም፡፡ ልባችን አብሮ የመኖር ሃውልቷን መገንባት አለባት:: እናም የዘመናችን ሃውልቶች “የባለጊዜ መዝረፊያ አህያም ብትሆን ሃውልት ይቆምልሃል” (ልብ ይበሉ የመቀሌውን አህያ ሃውልት)
አንተ እግዜሩ አገረ-ኢትዮጵ ሰው አጥታለችና አንተው ምራት!!===
Comments
Post a Comment