ጎጃም ልጃገረዶች የእንግጫ ነቀላና ከሰይ አጨዳ

 በግርማው አሸብር

ንግጫ ነቀላ መልከ ብዙ ሆነ ማህበራዊ ሚና እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሉት በጎጃም ማህበረሰብ ዘንድ ተወደደ በዓል ነው፡፡ አዲስ አመት ሲቃረብ ሰደጥ ሲሆን መስኩ፣ አረንጓዴ ሲለብስ ሜዳው፣ ተራራዎች በአበባ ሲያሸበርቁ ተስፋ የሚለመልምበት ፣ ወገን ከወገን ተነፋፍቆ የሚገናኝበት የደስታ ብርሃን የሚፈካበት ወቅት ምልክት ነው እንግጫ ነቀላ፡፡ ልጃገረዶች ከተፈጥሮ ጋር የሚገናኙበት፣ በተፈጥሮ ገጸ በረከት የሚፈነድቁበት ያም ሆኖ ከአበባው፣ ከሶሪት ላባው፣ በአደይ ሽታና መዓዛው ሁሉ ታድለው በእንግጫ በዓል ዜማ የሚጫወቱበት ሸጋ ወቅት ነው፡፡

ጎጃም ልጃገረዶች የእንግጫ ነቀላና ከሰይ አጨዳ በሚል ስያሜ የሚታወቀው የልጃገረዶች ጨዋታ የሚከበረው ነሐሴ ወር በተለይም የቡሄ ሰሞን ነው። ይህ ባህላዊ ጨዋታ የማህበረሰቡ ትውፊት ማንጸባረቂያ ሃይማኖታዊ እሴት ያለው ሲሆን በየአመቱ በመላው ጎጃም አካባቢዎች ይከበራል።በእንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ ለምልሞ አገፍግፎ የሚታይ አዲስ ሳር ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት የዕንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡

መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡
ራስ ላይ የታሰረው ደግሞ ለመስቀል በዓል ተቀምጦ ይቆይና ደመራው ላይ ታስሮ ቆይቶ እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ለራስ ምታትና ለጤንነት ሲባል በማኅበረሰቡ የሚከወን ነው፡፡
የእንግጫ ነቀላ በአል በጎጃም ከሚከበሩ የማይዳሰሱ ባህላዊ ሀብቶቻችን መካከል አንዱ ሲሆን በአሉ የሚከበረዉም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ነዉ፡፡ በዋዜማዉ እለት ልጃገረዶች ይሰበሰቡና ወደ አቅራቢያቸዉ በሚገኝ ረግረጋማ ወንዝ በመሄድ እንግጫ የሚባል የሳር አይነት፣አደይ አበባ፣ሶሪት አበባ ነቅለዉ ይዘዉ በጭፈራ ወደ ቤታቸዉ ይመለሳሉ እንግጫዉን ነቅለዉ እስኪመለሱ ወንዶች እየጨፈሩ ይጠብቋቸዋል፡፡

“እንግጫችን ደነፋ ጋሻዉን ደፋ”
“እንግጫችን የወሩ የቦረቦሩ”
“እንግጫየ ነዉ ብየ ጤፍ አረም ዉየ”
እንዲሁም ሴቶች እንደሚከተለው ይጨፍራሉ
“አደይ አበባ አደይ አደይ ፈነዳ”
“እንግዲህ ልቤ በአንድ ላይ ይራጋ”
” ተዉ አብራልኝ ዳቦት በናትህ ሞት”
“ተዉ አብራልኝ ተነሳ ወንድም ጎልማሳ
“አበራህልኝ ወይ ወንድሜ ሆይ” እያሉ ይዘፍናሉ::

ልጃገረዶች ብቻ እንግጫ ነቅለዉ አደይ አበባ ይዘዉ ወደየቤታቸዉ ይሄዳሉ።በዚያዉ ምሽትም ልጃገረዶች በአደይ አበባና በሶሪት አበባ እያዥጎረጎሩ አንድ ሜትር ርዝመት ያለዉን የእንግጫ ሳሩን ይጎነጉኑታል።

የዋዜማ እለት ወንዶች ልጆች ከስይ፣ዶግ፣ኮሸንድሬ እንጨቶችን በመልቀም ችቦ/ዳቦት ያዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ የእንጨት አይነቶች ለችቦነት ከተቀጣጠሉ በኋላ አይጠፉም አይጨሱም በመንደድ ረገድም ስለማያስቸግሩ በችቦነት ተመራጭ ናቸዉ። ያዘጋጁትን ችቦ ከቤት ለኩሰዉ ይወጣሉ።ችቦዉም ከቤት የሚለኩሱበት ምክንያት በቅድሚያ ለቤተሰቡ ብርሃን ሆነ የክረምቱ ጨለማ ወቅት አለፈ ብሎ አዲስ ዓመት መምጣቱን ለማብሰር ሲሆን በምሽቱ እዮሃ አበባዮ መስከረም ጠባየ በማለት በየወዳጅ ዘመድ ቤት በመሄድ እንጉሮገባሽ እያሉ የአዲስ አመት ብርሃን መምጣቱን በደስታ በችቦ ያበስራሉ። ባለቤቶች በአጸፋዉ በየአመቱ ያድርሳችሁ ይላሉ፡፡ ከዚያም ልጆች ተሰባስበዉ ችቦዉን በአንድ ቦታ ላይ በመሰብሰብ እሳቱን እየዞሩ ይጨፍራሉ።

በእንቁጣጣሽ እለት ልጃገረዶች በጠዋት ይነሱና የእንግጫ ጉንጉን ይዘዉ በተለያዩ ህብረ ዝማሬዎች በመታጀብ ተሰብስበዉ ወደ ቤተክርስትያን ይሄዳሉ፡፡ የያዙትንም የእንግጫ ጉንጉን ለቤተ-ክርስትያን ያበረክታሉ ፣ጉንጉኑን ያስራሉ፡፡ ከቤተክርስትያን መልስ ልጃገረዶች የእንግጫ ጉንጉን በመያዝ ወደ ዘመድ ወዳጅ ቤት በመሄድ እንቁጣጣሽ እንኳን አደረሳችሁ በማለት የእንግጫዉን ጉንጉን በቤቱ ምሰሶ ያስራሉ፡፡ ይህም ምሰሶ የቤቱ ዋና ማዕከል ስለሆነ ለቤቱ ልምላሜና ሰላምን ማብሰራቸዉን እንደሚያሳይ አባቶች ያስረዳሉ።

ባለቤቶችም በየአመቱ ያምጣችሁ ይሉና ቤት ያፈራዉን ዳቦ፣እንጀራ፣ቡቅር/ነጭ ጠላ/ ለልጆች ይሰጣሉ። እንኳን አደረሳቸሁ የሚለዉን ከጨረሱ በኋላ በእድሜ እኩያቸዉ ጋር በመሆን በቡድን ሆነዉ ይጨፍራሉ። በዚህን ጊዜ ጎረምሳዉ አይቶ የወደዳትን ልጃገረድ ይስማታል ወይም ሳማ በሚባል እሾህ ነካ ያደርጋታል፡፡ ይህም በወንዶች መርጨሻለሁ፣ ወድጀሻለሁ ስለዚህ ለትዳር እፈልግሻለሁ ማለት ነዉ።

እለቱም የፍቅረኛ መረጣ ቀን ስለሆነ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ ተብሎ ይታሰባል። ስለዚህ በዚህ ቀን ወጣት ልጃገረዶች እና ወንዶች ከብት፣ ቤት፣አዝመራ ወይም ሰብል መጠበቅ ተብሎ አይታሰብም። ይህ አዝመራ እና ሌላ የመጠበቅ ስራ ለዚያች እለት በወላጆቻቸዉ አልያም ደግሞ በአገቡ ወይንም በትዳር ላይ ባሉ እህት ወንድሞቻቸዉ/ቤተሰቦቻቸዉ/ እንዲሸፈን ይደረጋል። ምክንያቱም ቀኑ ለእነርሱ የነፃነት፣ የመደሰቻ ቀን ነዉና፡፡ በዚህን ጊዜ የተጀመረዉ የወጣቶች የአይን ፍቅርም ወደ ጋብቻ ያመራል። የእንቁጣጣሽ እለት በተለይ የበአላት ቀንን ተከትሎ ከሆነ በጣም ይደምቃል።

በእንግጫ ነቀላ በዓል አክባሪዎች ያላቸውን አለባበስ በጣም የባላገር ልብስ ይሁን እንጅ አዲስ ፈትል የፈረንጅ ክር በማሽን የተሰራ ሳይሆን በእጅ የተፈተለ ወይም በብልሃተኞች የተሰራ እንደሃገራቸው አዲሱን ለብሰው ያከብራሉ፡፡ ወንዶችም በተመሳሳይ ቁምጣ ሱሪ ለብሰው ከላይ ደግሞ ኩታ ደርበው ያከብራሉ፡፡
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡

‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡

በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡ይህም እንደ ገንዘብ ማግኛ ዘዴም ጭምር ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የተጀመረዉ የወጣቶች የአይን ፍቅርም ወደ ጋብቻ ያመራል። በመሆኑም የትዳር ጓደኛ መምረጫነትም ይጠቅማል፡፡ በጎጃ እንግጫ ነቀላ ከንፈር ወዳጅ መፈለጊያ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡

አንድ ህዝብ ባህልና ወጉ ሊጠበቅለት ፣ ሊለማለት ይገባል፡፡ ባህል የህዝቦች ህልውና ትልቁ ምልክታቸው ወይም ስለመኖራቸው ምስክር በመሆኑ ነው፡፡ ባህል ጥበብና ፍልስፍና ፣ ስነ እምነትና ስነህግ ነው፡፡ ባህል ያስማማል፡፡ ያዋድዳል፡፡ ህዝብንም ያለማል፡፡ ህዝብ ስነልቦናው የሚዳብረውና የሚበለጽገው በባህሉ ኩራትና ምጮት ሲሰማው ነው;፡፡ አሁን እንደምናየው ህዝቦች በመካከላቸው በባህላቸውና በእምነታቸው መሳደድ፣ መገደልና መፈናቀላቸው ደግሞ ሌላው የህዝቦች አለመታደል ነው፡፡

ታዲያ ጎጃ አንድም የባህለ፤ ማዕከልም ይሁን ቤተ ሙዚየም የላችም ፡፡ የባህልና የሃገርበቀል እውቀት ባለጸጋው ታላቁ የጎጃም ህዝብ ባህልና ወጉን የሚያለማበት፣ የሚያበለጽግበትና ሚያሳድግበት መድረክ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይልቁንም የጎጃም ማንነት በአንዳንድ ከተሜ ቀመስ አካባቢዎች በሚሰሬ ተማጅ ቴአትር አዘጋጆች ጎጃሜነት በገጸ ባህሪነት እንደ ኋላቀር እና ሞኝ ምንም ያልተማረ ተምሳሌትነት ገብቶ ይስተዋላል፡፡ እንዲለማ በስርዓተ መንግስት ውሥጥ ላልተደገፈ እዝብ እጣፋንታው ይሄ ይሆናል፡፡ በአብረ ማርቆስ ከተማ ሊሰራ ታስቦ ከአስር አመት በፊት የተጀመረው ባህል ማዕከል ቀርቶ በዚያ ቦታ የምስራቀቅ ጎናም ዞን አዳራሽ እየተገነባ ነው፡፡ ህዝቡ አዳራሽ ሳይሆን ባህል ማዕከል እተሰራልኝ ነው ብሎ ነው የሚያውቀው የተነገረውም፡፡

የርዕሴ መነሻ ወቅታዊውን የእንግጫ ነቀላ በዓል ምንነት አጭር መረጃ መስጠት ሆኖ እያለ ስለጎጃም ህዝብ ህልውና ሳስብ ግን ብዙ ነገር ለማለት ይዳዳኛል፡፡ አስባለሁ፡፡ ጎጃሜ አማራ ነኝ፡፡ በድምር ውጤቱ በጎጃሜነት የተወጠንሁ፣ በአማራነት የፋፋሁ በኢትዮጵያዊነቴ የደረጀሁ ብርቱ ዜጋ ነኝ፡፡ ግን ተወጠንሁበት ጎጃም በስነጽሁፍ፣ በሃገር በቀል እውቀት፣ በታላላቅ ሃገር ባላደራ ግዙፍ ዜጎች መነሻ የአርበኛው ጎጃም ትውልድ እራሱ እንዳይለማ፣ ባህሉ እንዳያድግ፣ ኢኮኖሚው እንዳያንሰራራ የፈረደበት ማን ይሆን?

ለጊዜው መልሴ እኔ ዝም ካልሁ ማንም የሚሰጠኝ እድል እንደማይኖር እገነዘባለሁ፡፡ በጎጃም ህዝብ ላይ የሠለጠነ፣ ያደገ፣ የተጠቀመ ሁሉ ስለጎጃም ህዝብ ያገባዋል፡፡ ስለሆነመው ጎጃም እራሱ ስሙና ዝና ብቻውን |የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ቅርስ ነውና ልንበረታ ፣ ወቅቱን ልንዋጅ ይገበናል፡፡

መልካም የእንግጫ ነቀላ በዓል

Comments